skip navigation

የኳስ ንግሥና የኢትዮጵያውያን አመታዊ በአል

By Redeat Bayleyegn, 06/20/15, 6:00PM EDT

Share

የ32ኛው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ አመታዊ ቶርናመንት ደረሰ። ከጁን 28 እስከ ጅላይ 4 2015 በዩኒቨርስቲ ኦፍ ሜሪላንድ በርድ ስቴድየም ይካሄዳል። 31 ቡድኖች ከ25 የሰሜን አሜሪካ ከተሞች ለውድድሩ ይመጣሉ ፥ ካልጋሪና ቶሮንቶ ካናዳን ጨምሮ።

በቀላሉ መገመት እንደሚቻለው እያንዳንዱ ቶርናመንት ይዞት የሚመጣው የራሱ የሆነ ክስተት አለው። ለዚህ ነው ብዙዎቻችን ወደዚህ ውድድር በየአመቱ ብንሄድም የማይሰለቸን። በአመቱ አጋማሽ ላይ "ዘንድሮስ ሌላ ቦታ ነው ለዕረፍት የምሄደው" ብሎ ዝቶ ቶርናመንቱ ሲቃረብ የአየር ትኬቱን ቆርጦ ከች የሚለው ብዙ ነው።  ዘንድሮም የተለየ እንደማይሆን ጥርጥር የለውም። በተለይ ከእግርኳሱ ዙርያ የሚደረጉት የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶች "የማይቀርባቸው" ናቸው። ዘንድሮ የጎልፍ ውድድርም ይኖራል ፤ ከዚህ በፊት አንድ ግዜ ብቻ የተሞከረ ስፖርት ነው። መካፈል የሚፈልግ ሰው አሁንም መመዝገብ ይችላል። ለማንኛውም ተጨማሪ መርጃ www.esfna.net በመሄድ ማግኘት ይቻላል።

የዚህ መጣጥፍ ትኩረት ግን ስለዘንድሮው የእግርኳስ ውድድር ነው። ብዙ ግዜ ከኳሱ አካባቢ ራቅ የምትሉት ሰዎች የማታውቋቸውን ነገሮች ታገኙበት ይሆናል።

ፌዴሬሽኑ በ1984 ሲጀመር 4 ቡድኖች ቢጀምሩትም ዛሬ 31 ደርሷል። በቅርቡም 32 ይሆናል፤ በተለያየ ከተሞች የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ካሁኑ ፍላጎታችሁን ብታሳዩ 32ኛው ቡድን የመሆን እድላችሁን ታሰፉታላችሁ።

31 ቡድኖች ደግሞ በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍለዋል። አንደኛ ዲቪዚዮን 16 ቡድኖች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ 15 ቡድኖች አሏቸው። በሁለቱም ዲቪዚዮኖች አራት ምድቦች አሉ። እያንዳንዳቸው 4 ቡድኖች ሲኖሯቸው ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ አንዱ ምድብ 3 ቡድኖች ብቻ አሉት። ባለአራት ቡድኖች ምድብን እንደመሰረት አድርጋችሁ አስቡትና እንግዲህ በመጀመሪያው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች እያንዳንዱ ቡድን 3 ጨዋታዎችን ያደርጋል ማለት ነው። በፌዴሬሽኑ ውድድር ግማሽ ፍፃሜ ስለሌለ ወደሩብ ፍፃሜ የሚያልፉት የየምድቡ አሸናፊዎች ብቻ ናቸው። ይሄ ለምን ሆነ? ካላችሁ ዋናው ምክንያት ውድድሩ የአንድ ሳምንት ብቻ ስለሆነ የግዜ ጉዳይ ነው። መፍትሄ ማግኘት ቢቻልም መፍትሄዎቹ ይዘዋቸው የሚመጡትን የተለያዩ ሁኔታዎችን ተመልክቶ ፌዴሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ፋይሉን ዘግቷል።

እሁድ የሚጀምረው ውድድር የምድብ ውድድሩን ሃሙስ ሲጨርስ 46 ግጥሚያዎች ተደርገዋል ማለት ነው። አንባቢ ቆም ብሎ ቢያስበው ይህ ማለት በቀን ቢያንስ ዘጠኝ ጨዋታ ማለት ነው። እያንዳንዱ ቡድን በአምስት ቀን ውስጥ ሶስት ጨዋታዎች ያደርጋል። ደግነቱ ጨዋታዎቹ 90 ሳይሆን 70 ደቂቃዎች ብቻ ናቸው። ቀላል እንዳይመስላችሁ። የጊዜው ማጠር ጨዎታዎቹን በጣም ፈጣን እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በቅድሚያ ጎል የሚያገባን ቡድን ሃያላዊነት ስለሚሰጠው ባላጋራውን ይባስ በርትቶ እንዲጫወት ያስገድደዋል። የሆነው ሆኖ በማንኛውም መስፈርት ሶስት ጨዋታ በአምስት ቀን አድካሚ ነው። በተለይ ራሱን አዘጋጅቶ ላልመጣና ጎበዝ ስለሆነ ሁሉንም ጨዋታ እንዲጫወት ለሚጠበቅበት ተጫዋች። ከዚህም ጋር ተያይዞ ይሄንን ሁሉ ጨዋታ ማስተናበሩ፤ በቂ ዳኞች መቅጠር ፣ በሰአቱ ውድድሮቹ መካሄዳቸውን ማረጋገጥ ፣ ከጨዋታው ጋር የተያያዙ ስታትስቲክሶችን መመዝገብ ፤ ኧረ እንደው በቀላሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ኳሶችን ማዘጋጀት ራሱ ፌዴሬሽኑ ለ32 አመታት በበጎ ፈቃደኞች የሚያከናውነው ነገር ነው። ተመስጋኙ ብዙ ነው።

ወደዘንድሮ ውድድር "ማን ያሸንፍ ይሆን?" ግምትና ትንቢት ከመግባታችን በፊት ውድድሩ ሲደርስ በየቡድኑ ስለሚደረጉ አንዳንድ ጉዳዮች እናንሳ።

በፌዴሬሽኑ ህግ መሰረት ቡድኖች ተጫዋቾቻቸውን በJune 15 ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል። ቢያንስ ከሚፈቀደው 25 ተጫዋቾች 15 ተጫዋቾች መመዝገብ ግዴታ ነው። የቀረ ካለ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ባለው እኩለሌሊት በተጫዋች 20 ዶላር መቀጫ ከፍሎ ማስመዝገብ ይቻላል። የህጉ መንፈስ በJune 15 ተጫዋች ያላስመዘገበ ቡድን ውድድሩን ለመካፈል እንዳልቻለ መቆጠር ቢሆንም እስካሁን ግን ፌዴሬሽኑ ለውንድማማችነት ሲል በዝምታ ያልፈዋል። ወደፊት ግን ለውጥ ይኖራል። ቡድኖች በጊዜ ገደቡ ከማያስመዘግቡበት ምክንያቶች አንዱ ወደ ውድድር የሚሄዱ ተጫዋቾችን በግዜ አለማውቅ ይገኝበታል። ዋናውን ምክንያት እዚህ አንነካውም። ውድድሩ ሳምንታት እንኳን ቀርተውት በስራ ፈቃድ ማጣት ፣ በቤተሰብ ፣ በፋይናንስ ፣ በትምህርትና ሌሎች ምክንያቶች ተጫዋቾች መሄድ እየፈለጉም ሊቀሩ ይችላሉ። አንዳንድ ደግሞ ወጪውን ችለው መሄድ የማይችሉ ልጆች አሉ። ሌሎች ተጫዋቾች እንዲሁም አሰልጣኞች ደግሞ አሉ "ካልተከፈለኝ አልሄድም" የሚሉ። እነኚህን አይነቶችን ሲለማመጡ ወይንም ወጪን ለመሸፈን የተለያዩ መፍትሄ የሚፈልጉ የቡድን መሪዎች ሁሉም ቡድን ውስጥ አሉ። ቡድን መምራት ራስ ምታት ይሰጣል ፤ ተጫዋች መሆንም እንዲሁ። ይህ ወጭ እንጂ ገቢ የሌለው ውድድርን የሚያደምቁት ተጫዋቾችና የቡድን መሪዎች ምስጋና ይድረሳቸው። ይህን የሚያደርጉት ለኳስ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትንም ብለው ነውና። 

ስለዚህ አንባቢ ሆይ፦ ቡድን ማዋቀርና ከአገር አገር ለውድድር ማዟዟር ቀላል ነገር ስላይደለ በአካባቢህ ያለውን ፥ ከተማህን ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ቢቻል በቋሚነት ባይቻል ደግሞ እርዳታህን ባይጠይቁህም ለግስ!

እንግዲህ አይቀርምና ጨዋታው ደርሷል። ሁሉም አቋሙን ያውቀዋል። "ዘንድሮ ዋንጫው የኛ ነው!" የሚለው ፉከራ በሁለተኛው ጨዋታ ቁርጡ ይለያል። በአንደኛ ዲቪዚዮን ስለዋንጫ መብላት የነበረው ግርግር "ስለአለመውረድ" በሚለው ይተካል። ከላይ ሁለት ዲቪዚዮን ያልኳችሁን አስታውሱ። በፌዴሬሽኑ ህግ መሰረት በውድድሩ መጨረሻ በአንደኛ ዲቪዚዮን 15ኛና 16ኛ ሆነው የሚጨርሱ ቡድኖች እጣ ወደሁለተኛ ዲቪዚዮን መውረድ ነው። ወደሲኦል የመውረድንም ያህል ባይሆን ማንም የማይመኘው እጣ ነው። ሁለተኛ ዲቪዚዮን ማለት ከፌዴሬሽኑ የሚገኘውን ጥቅማጥቅም ባይቀንሰውም ልክ ክፍል እንደመበወዝ (መድገም) አይነት ስሜትን ይፈጥራል። በዚያው መጠን ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ወደአንደኛ ዲቪዚዮን ለመግባት ያለው ውድድር እንዲሁ ከፍተኛ ነው። ወድገነትም የመግባት ያህል ባይሆንም አንገት ቀና የሚያስደርግ ስኬት ነው።

ትንበያ!

መጀመሪያ ስለአንደኛ ዲቪዚዮን እናንሳ። ፌዴሬሽኑ በሁለት ፥ በምዕራብና ምስራቅ ምድቦች የተከፈለ ነው። ይህንን ይዘን ከታሪካዊ እውነት ብንነሳ የዘንድሮውን ውድድር የሚያሸንፈው ቡድን የሚሆነው ከምስራቅ (Eastern Conference) ነው። ሲጀምር ከ16ቱ ቡድኖች ስድስቱ ብቻ ናቸው ምዕራባዊ። ገና ከጅምሩ 38% እድል ይዘው ነው የሚነሱት። ከስድስቱ ውስጥ አንዱ ብቻ ነው ዋንጫ በልቶ የሚያውቀው ፥ ሎስአንጀለስ ስታርስ። በምስራቅ አሜሪካ ከተደረጉ 15 ውድድሮች 14ቱን የተቀራመቱት ምስራቃዊዎቹ ናቸው። አንዷንም የወሰዳት ሎስአንጀለስ ስታርስ ሲሆን ዘመኑም በ1988 የዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በተደረገ ውድድር ነበር። ስለዚህ ሚዛኑ ገና ከጅምሩ 99.93% ለምስራቆች ያጋድላል። ዘንድሮ የሚደረገው ውድድር ለዲሲ አካባቢ 8ኛው ሲሆን ከ7ቱ ውድድሮች 5ቱን የወሰዱት በዚያ አካባቢ ካሉት 5 ቡድኖች ሶስቱ ናቸው። ዋሽንግተን ዲሲ ስታርስ 3 ግዜ ፣ ቨርጂኒያ ላየንስና የዋሽንግተን ዲሲ ዩኒቲ አንድ ፥ አንድ ግዜ። በቀደመው ታሪክ ከሄድን ሌሎች ቡድኖች ዋሽንግተን አካባቢ መጥተው ዋንጫ የማንሳት እድላቸው ከ30% ያነሰ ነው። ጀርመንም በምዕራቡ ሄሄምስፊር መጥታ ብራዚል ላይ የአለም ዋንጫ በልታለች። ስታትስቲክሱ እንዲያውም እዚህ እኛ ጋር ይሻላል። አንድ ተጨማሪ ስታትስቲክስ ልጨምር ፥ ከፌዴሬሽኑ 31 ቀደምት ውድድሮች 14ቱ ዋንጫዎች በአራት የዲሲ አካባቢ ቡድኖች ተወስዷል ፤ 45% ማለት ነው። ከዲሲ ወጭ ለሚመጡ 11 ቡድኖች ይህን ስታትስቲክስ እንኳንስ ሊያስጨንቃቸው ከነጭራሹም አስበውበትም አያውቁም። ውድድሩ ሲያልቅ ግን እውነታው ከዚህ የሚርቅ አይመስለኝም። ዲሲ ስታርስ ለስምንተኛ ፣ ሜሪላንድ ለአራተኛ ፣ ዲሲ ዩኒቲ ለሁለተኛ ፣ ሜሪላንድ የቅዱስ ሚካኤል ለመጀመሪያ ግዜ ዋንጫ ለማስቀረት እየተዘጋጁ ይገኛሉ። የቨርጂንያ ላየንስ ቡድን ደግሞ ያለፉትን ሁለት ውድድሮች ስላሸነፈ በፌዴሬሽኑ ታሪክ ተደርጎ የማያውቀውን ለሶስት ተከታታይ ግዜያት ዋንጫ ለማንሳት ተዘጋጅቷል። ቀላል አይሆንም። ያንን ማድረግ ከቻሉ በአጠቃላይ የአራት ውድድሮች አሸናፊ ይሆናሉ ማለት ነው።

ከምዕራቦች ታሪክ ሰሪ ቡድን ከወጣ በኔ ትንቢት ሎስአንጀለስ ስታርስና ሲአትል ባሮን ቀደም ብዬ አነሳለሁ። ሎስአንጀለስ ዳሎል ፣ ካልጋሪ ፣ ሳን ሆዜ አንበሳና ኦስተን ብሉ ናይል ደግሞ በጉዳዩ የሚሉት ይኖራቸዋል።

የቀሩት የምስራቅ ቡድኖች ቶሮንቶ ፣ ኒው ዮርክ ፣ አትላንታ ፣ ቦስተንና ኦሀዮ ናቸው። ቶሮንቶ ያለፈው አመት ሁለተኛ ፥ ኦሀዮ ደግሞ ሶስተኛ ነበር የወጡት። በዚህም አመት ዋንጫ ለመውሰድና ከዚህ በፊት ያሸነፉትን ቁጥር ወደሁለት ከፍ ለማድረግ የተቻላቸውን እንደሚጥሩ ይጠበቃል። ዝነኛው የአትላንታ ቡድን ባለፉት ሁለት አመታት ወደሁለተኛ ዲቪዚዮን ከመውረድ ተርፏል። ቦስተን ከሁለት አመት በፊት ጥሩ ቡድን አዘጋጅቶ ሁለተኛ ወጥቶ ነበር። ኒውዮርክ ይህን ያደርጋል ብሎ መጠበቅ ይከብዳል። ነገር ግን በየአመቱ ይህ ውድድር ያልተጠበቁ ክስተቶችን ያመጣል። ወደታች ዲቪዚዮን ላለመውረድም ዋንጫን ለማስቀረት ከሚደረገው ፉክቻ አይተናነስም። ኳስ ለምንወደው አጓጊ ኩነቶች የሞሉት ውድድር ነው!

የሁለተኛ ዲቪዚዮን ውድድር የሚያተኩረው "ወደአንደኛ ዲቪዚዮን ማን ይመጣል?" በሚለው ግምት ዙሪያ ነው። በዘንድሮው ውድድር ዴንቨር ፣ ሳን ዲያጎ ፣ ሂውስተንና ሳንፍራንሲስኮ ላይ ከፍተኛ ግምት መጣል ቢቻልም ካንሳስ ሲቲና ፍላዴልፊያም ብርቱ ተፎካካሪዎች ይሆናሉ። ሌሎችም ለዝግጅቱ በራቸውን ዘግተው እየሰሩ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።

በመጨረሻ በኔ ግምት ከአንደኛ ዲቪዚዮን ቨርጅንያን ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ሳን ዲያጎን መርጫለሁ። ለሁሉም ቡድኖች ግን መልካም እድልን እመኛለሁ። በሰላም አድርሶ በሰላም ይመልሳችሁ።

በየመሃሉም የሴቶችና የህፃናት እግርኳስ ውድድሮች ይኖራሉ። የፌዴሬሽኑ ግብዣ ለሁሉም ስለሆነ እንግዲህ እንዳትቀሩ። የማይቀርበት ውድድርና ቁምነገሮች ይጠብቋችኋል።

ረድኤት ባይለየኝ
ዳላስ ፥ ቴክሳስ

ለፀሃፊው አስተያያት ካላችሁ ውድድሩ ድረስ በመምጣት በግንባር ማቅረብ ይቻላል።